ከፊታችን አርብ ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው በአሽከርካሪዎች ላይ የሚደረግ የአልኮል መጠን ምርመራ ሊጀመር መሆኑ ተገለፀ።

(ታህሳስ 26/2015 ዓ.ም) በአዲስ አበባ ከሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት መንስኤያቸው ጠጥቶ ማሽከርከር እና ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር መሆኑን የትራፊክ አደጋ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ እንደገለፁት ከመንገድ ትራፊክ አደጋ ዋና ዋና መንስኤዎች መካከል የተጋላጭነት ምክንያት የሆኑት ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶ አለመጠቀም፣ ሄልሜት አለማድረግ እና የህፃናት ደህንነት መጠበቂያ መሣሪያ አለመጠቀም መሆናቸዉን በመጥቀስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የጠጥቶ ማሽከርከር ቁጥጥርን ጨምሮ በተጠናከረ ሁኔታ ለመስራት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የጋራ እቅድ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡

የጠጥቶ ማሽከርከር ቁጥጥሩ በኮቪድ 19 ምክንያት ለሁለት ዓመታት መቋረጡ በትራፊክ አደጋ የሚደርሱ ጉዳቶች ቁጥር መጨመር ላይ የራሱ አስተዋፅኦ እንደነበረው ጠቁመው አሁን ቁጥጥሩ መጀመሩ ችግሩን የሚቀርፍ እንደሆነ በተጨማሪም ከፊታችን የሚከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላት ላይ የትራፊክ አደጋ እና መጨናነቅ እንዳይፈጠር እንደሚሰራም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሸዋይርጋ ግዛው በበኩላቸው በመግለጫው እንዳሉት የጠጥቶ ማሽከርከር ቁጥጥር መጀመሩ በትራፊክ አደጋ የሚቀጠፈውን የሰው ልጅ ህይወት ቁጥር ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

ከፊታችን የሚከበሩ ሁለት ታላላቅ ኃይማኖታዊ በዓላት ላይ የትራፊክ ፍሰት እና ደህንነቱን በማረጋገጥ

የከተማዋ ነዋሪዎች በበዓላት ወቅት ለመዝናናት ሲባል የአልኮል መጠጥ ወስደው የሚያሽከረክሩ ሰዎች እራሳቸው እና ለሌችንም ከትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ ጥንቃቄ ማድግ እዳለባቸው በማሳሰብ ከጠጡ በፍፁም እንዳያሽከረክሩ፣ ካሽከረከሩ ደግሞ በፍፁም መጠጣት እንዳሌለባቸው መልዕክት አስተላፈዋል፡፡

ኤጀንሲው እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን በጋራ ባዘጋጁት እቅድ የቁጥጥር ስራው የሚከናወንባቸው ቦታዎች የኦፕሬሽኖቹ ቀንና ሰዓት በግልፅ በዕቅድ የተቀመጠ በመሆኑ ስራዎቹ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ከታህሳስ 28/2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚከናወንም ይፈ ተደርጓል ።

ኤጀንሲው በከተማዋ ሰለማዊ እና ተቀባይነት ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴን ለማረጋገጥ ከቁጥጥር ስራዉ ባሻገር የመንገድ ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እና በምህንድስናው ዘርፍ በርካታ የማሻሻያ ስራዎችንም እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

@TMA

Leave a Reply