(የካቲት 12/2016 ዓ.ም):- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ከትራንስፖርት ቢሮ እና ብሉምበርግ ኤኒሸቲቪ ፎር ግሎባል ሮድ ሰፍቲ ጋር በመተባበር ከኬንያ ሞምባሳ ለመጡ የከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች የልኡካን ቡድን አባላት በከተማዋ እየተካሄደ ስላለዉ የመንገድ ደህንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ልምዶቹን አካፍሏል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ የልምድ ማካፈል መርሃ ግብሩን በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት ከዛሬ የተወሰኑ አመታት በፊት የመንገድ ትራፊክ እንቅስቃሴ እና ደህንነት በከተማዋ እጅግ አሳሳቢ እንደነበርና በከተማ አስተዳደሩ ይሁንታና ለዘርፋ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እንዲሁም ባለድርሻና አጋር አካላት ትብብር የከተማዋ የመንገድ ደህንነትና የትራፊክ እንቅስቃሴ ትርጉም ባለው መልኩ መሻሻል አሳይቷል።
በማያያዝም ስለ ትራንስፖርት ቢሮ እና ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን መዋቅር አደረጃጀት እና አጠቃላይ በከተማዋ የትራንስፖርት ስርዓትና ተግባራት ዙሪያ በጥልቀት የዳሰሱ ሁለት ሰነዶች ለልኡካን ቡድኑ አባላት በማብራሪያነት ቀርበዋል።
እንዲሁም የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ እና የትራፊክ መረጃ አያያዝና አተናተን ዙሪያ በደብሊው አር አይ እና ቫይታል ስትራቴጂ በተባሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ሁለት አስረጂ ሰነዶች በተከታታይ ቀርበዉ አባላቱ ልምዱን እንዲወስዱ ተደርጓል።
በመጨረሻም በሁሉም ሰነዶች ላይ ልኡካን ቡድኑ አባላት ሃሳብ አስተያየት እና ጥያቄዎችን አንስተው ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በከተማዋ በመንገድ ደህንነትና ፍሰት ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን የመስክ ጉብኝት በማድረግ የልምድ ማካፈሉ መርሐ ግብር ተጠናቋል።
ምንጭ:-@TMA