እናመሰግናለን!!

ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

በከተማችን አዲስ አበባ “የሆራ ፊንፊኔ ” የኢሬቻ በአል ባማረና በደመቀ ባህላዊ እሴቱንና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ተከብሮ በሰላም ተጠናቋል፡፡

ከለዉጡ ወዲህ ለ4ኛ ጊዜ በከተማችን አዲስ አበባ የተከበረውና በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የተሳተፈበት የዘንድሮው የሆራ ፊንፊኔ በዓል ገና ከዋዜማው ጀምሮ ባማረ ድባብ፣ በከፍተኛ ድምቀትና ውበት፣ በእንግዳ ተቀባይነት ስሜት ባህላዊ እሴቱንና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ ያከበርነው፣ ትብብራችን ጎልቶ የወጣበት፣ ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና ህብረብሄራዊነት ደምቆና ፈክቶ ድንቅ የበዓል አከባበር የታየበት ነው፡፡

አሸባሪ ቡድኖች በቀቢፀ ተስፋ በጦር ሜዳ የደረሰባቸውን ኪሳራ ለማካካስ በከተማችን የተከበረው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የሁከት ማእከል ለማድረግ በተጨባጭ ቢንቀሳቀሱም፣ በሰላም ወዳዱ ህዝብ፣ በፀጥታ ሃይሎችና ህዝባዊ ሰራዊታችን እንዲሁም በአመራሩ ቅንጅትና ትብብር የጥፋት ህልማቸውን በማክሸፍ ሰላማዊና የተረጋጋ በዓል ማክበር ተችሏል።ለዚህም እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ!!

ይህ በዓል ስኬታማ እና ያማረ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ዋናውንና የማይተካ ሚና የተጫወተው የአዲስ አበባ ህዝብ ትልቅ ምስጋና ይገባዋል፡፡ከተማዋን ከማስዋብ እና አካባቢን ከማፅዳት ጀምሮ እንግዶቹን በየአካባቢው ባማረ መስተንግዶ በመቀበል፣በዓሉ ሰላማዊ ድባቡን ይዞ እንዲጠናቀቅ መንደሩንና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ፣ የፀረ ሰላም ሃይሎችን በያሉበት አጋልጦ በመስጠት ላበረከተው አስተዋፅኦ ከልብ እናመሰግናለን!!

አባገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎች፣ ቄሮዎች፣ ቀሬዎች እና ፎሌዎች ይህ በዓል እሴቱንና ስርዓቱን ጠብቆ በከፍተኛ ድምቀትና ሰላማዊነት እንዲከበር ስላደረጋችሁ እናመሰግናለን፡፡

በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በበቂ ዝግጅትና በሀላፊነት ስሜት በብቃት ለሰራችሁ መላው የከተማችን የጸጥታ አካላት፣ የሰላም ሰራዊት አባላት እንዲሁም የደንብ ማስከበር አገልግሎት ምስጋናችንን እናቀርባለን!!የከተማችን አዲስ አበባ ወጣቶች በዓሉ በመከባበርና በመተሳሰብ በአብሮነት እንዲከበር ስላደረጋችሁ እናመሰግናለን፡፡

በየደረጃው የምትገኙ አመራሮች ይህ በዓል ያለአንዳች እክል በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ በትጋትና በንቃት በየተመደባችሁበት ሃላፊነታችሁን ስለተወጣችሁ እናመሰግናለን!!

ወደከተማችን በዓሉን ለመታደም የመጣችሁ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህ በዓል የጋራችን መሆኑን በተግባር በማረጋገጥ ላሳያችሁት ታላቅ የአብሮነት ተምሳሌትነት እንዲሁም ለከተማችን ሰላም ለነበራችሁ ሚና እናመሰግናለን!!

የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለማበላሸት የሚፈልጉ የውጪ ሃይሎች በዚህ በዓል እንከኖችን በመፈለግ የሃገራችንን ገፅታ ለማበላሸት ቢቋምጡም አጠቃላይ የሚድያ ተቋማትና የሚድያ ባለሙያዎቻች ትክክለኛ የበዓሉን መልካም ገፅታ አጉልታችሁ ስለዘገባችሁና የህዝቡን አብሮነት በሚገባ ስላሳያችሁ እናመሰግናለን!!

አሁንም ቢሆን እንግዶቻችን እንዳመጣጣቸው ወደየአካባቢው በሰላም እስኪመለሱ ድረስ በተጀመረው የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት እስከመጨረሻው ድረስ በትጋት እና በቅንጅት መስራታችንን እንድንቀጥል እና በነገው እለት የሚከበረው የሆራ አርሰዴ በዓልም በሰላም እንዲጠናቀቅ ፣ ሁላችንም ይበልጥ ተጠናክረን በትብብርና በሃላፊነት ስሜት ሃላፊነታችንን እንድንወጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ!

#በድጋሚ_ለሁላችንም_መልካም_የኢሬቻ_በዓል_ይሁንልን!

Leave a Reply