አዲስ አበባ፤ ህዳር 26፤ 2015 ዓ.ም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በዓለም ለ19ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ-ሙስና ቀን “ሙስናን መታገል በተግባር” በሚል መሪ ቃል ከአጠቃላይ የትራንስፖርት ቢሮ ሰራተኞች ጋር የቢሮው ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ በውይይቱ እንደተናገሩት ሌብነትን በተግባር በመታገል ረገድ ሁሉም የቢሮው ሠራተኞችና አመራሮች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡
አያይዘውም በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን፣ ለሌብነት የሚያጋልጡ ጉዳዮችን ጭምር በመለየት የተግባር ትግል ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
በትራንስፖርት ቢሮ የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አምባላይ ዘርዓይ በበኩላቸው በፀረ-ሙስና ዙሪያ የውይይት ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በሰነዱም ስለ ሙስና ጉዳትና አስከፊነት በዓለም ብሎም በሀገራችን የሚያደርሰውን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስና ጉዳት አንስተዋል፡፡
አቶ አምባላይ አክለውም ሌብነት ለሰው ልጆች ነቀርሳ፤ የሀገራችንን ልማት የሚያዳክም፤ የኢኮኖሚ እድገትን የሚገታ፤ የሰውን ልጅ ሞራልና ስነ ምግባር የሚያኮስስ፤ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚያደርግ መጥፎ በሽታ በመሆኑ ሁላችንም በአንክሮ በመረዳት መታገል ይገባናል ብለዋል፡፡
ሁሉም የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች በህዝብ የተሰጠንን ስልጣንና ሃላፊነት በአግባቡ በመፈፀምና በማስፈፀም በጋራ በመስራት ሙስናን መታገል እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
በተለይ ደግሞ የፍትህ አካላት ከፀረ ሙስና ተቋማት፤ ከዜጎች፤ ከመገናኛ ብዙሃንና ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በጋራ በመስራት በሀገራችን በሙስና ምክንያት የሚደርሰውን ያላስፈላጊ ውድመትና የህዝብ እሮሮ በመታደግ ሀገራችን ኢትዮጵያ የሠላምና ከሙስና የፀዳች ሀገር እንድትሆን መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ተሳታፊዎችም ሌብነትን ለመታገል ከቃል ንግግር ባለፈ የተግባር ትግል እንደሚያስፈልግ በማውሳት በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የፀረ-ሌብነት ትግል አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች፣የቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች፣ የፌደራል የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተወካይ፣ ከ850 በላይ የሚሆኑ የቢሮው የማዕከልና የቅርንጫፍ ሰራተኞች በእለቱ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡