ባለፉት ስድስት ወራት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የትራንስፖርት ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱ ተገለፀ።

ቢሮው የ2015 በጀት ዓመቱ የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀሙን ከዘርፉ ተጠሪ ተቋማት ጋር በጋራ ገምግሟል።

============

አዲስ አበባ፣ ጥር 9 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በ2015 የግማሽ በጀት ዓመት ከተጠሪ ተቋማቱ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎትና የቀላል ባቡር አገልግሎት ድርጅት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የትራንስፖርት ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ተገለፀ።

ቢሮውና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች የ2015 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀረበው ሪፖርት ላይም ውይይት ተደርጓል።

በሪፖርቱም በእቅድ ተይዘው የተከናወኑ ተግባራትንና እቅድ አፈጻጸማቸውን የተገመገመ ሲሆን፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተሰሩ ስራዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ ብልሹ አሰራርን በመታገል የተጠያቂነት ስርዓት በመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ እንደነበር ተገልፆል፡፡

በተመሳሳይ በትራፊክ አደጋ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት፣ የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ክፍያ እንዲፈፅሙ መደረጉ፣ በተመረጡ 26 መጋጠሚያዎች እና አደባባዮችም ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የማሻሻያ ስራዎች እየተሰራ መሆኑ፣ ለአውቶብስ ብቻ የተለዩ መስመሮችን ቁጥጥር በማድረግ የታለመላቸውን አገልግሎት እንዲውሉ መደረጉ እንዲሁም የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በተያያዘ ሞዴል ተቋማትን መፍጠር መቻሉ፣ (VIP) መስኮቶች በልዩ ሁኔታ ለሚስተናገዱ መዘጋጀቱና አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ምሳ ሰዓትን ጨምሮ አገልግሎት በመስጠት በግማሽ የበጀት ዓመት 665,742 ተገልጋዮችን በማስተናገድ ከተለያዩ የአገልግሎት ዘርፍ በአጠቃላይ ከ 1.4 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በዋናነትም በአማካይ በየቀኑ 9,657 ተሽከርካሪዎች ማሰማራት መቻሉን፣ ባለው የአቅርቦት መጠን በቀን 3.1 ሚሊየን ጉዞ መፈጠር መቻሉንና በ33 ሺ 298 ስምሪት ያልገቡ አጥፊ አሽከርካሪዎች እርምጃ በመውሰድ 24 ሚሊዮን ብር መሰብሰብን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በባቡር መሰረተ ልማት ላይ በተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ መከሰት፣ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት መቆራረጥ እንዲሁም የባቡር መሰረተ ልማቶች ላይ በተለይ የኤሌክትሪክ እና የሲግናል ገመዶች ስርቆት መፈጸምና በህዝብ ትራንስፖርት መጠለያዎችም ላይ እየተፈፀመ ያለ ህገ- ወጥ ተግባር ለአገልግሎት አሰጣጡ ችግር እንደነበር በሪፖርቱ ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በስድስት ወሩ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆኑን በመግለፅ፤ በዋናነትም ህዝብ የሰጠንን ኃላፊነት በጊዜ የለኝም ስሜት ወደ ጎን መተው ትክክል አይደለም ብለዋል።

በተጨማሪም በቀጣይ ቀሪ ስድስት ወራት በእቅድ ተይዘው ያልተከናወኑ ተግባራትን በእቅድ በመያዝ አሁን እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦችን ማስቀጠል እንደሚገባ እንዲሁም፤ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን የከተማዋን እድገት የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ በአንክሮ ገልፀዋል፡

Leave a Reply