(የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፤ ሚያዝያ 04/2016ዓ.ም) የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የመገናኛ አካባቢን የትራፍክ ፍሰት ለማሻሻል እንዲሁም ከተርሚናል ወደ ተርሚናል የሚደረግ የእግረኞች እንቅስቃሴን ለመቀነስ ከወርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲቲዩት (WRI) በጋራ ያጠናውን የጥናት ፕሮጀክት ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት በዘርፉ ካሉ ባለሙያዎች ጋር የጋራ ውይይት አደረገ።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዳዊት ዘለቀ ጥናቱን ማድረግ ያስፈለገበት ዋነኛ ዓላማ መገናኛ አከባቢ የሚታየውን የእግረኛ ፍሰት ለመቀነስና ለማሻሻል ነው ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም መገናኛን ነክተው የሚተላለፉ የብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን መነሻና መድራሻ ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም የነባር የብዙሃን ትራንስፖርት መስመሮች ላይ የአውቶብስ ቁጥር በመጨመርና አደዲስ የብዙሃን ትራንስፖርት መስመሮችን በመጨመር በጥናቱ መነሻነት በቀጣይ በሙከራ ደረጃ ወደ ስራ የሚገባ ይሆናል ብለዋል።
የወርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት /WRI/ ኮንሰልታንት የሆኑት ኢንጂነር አሹ ስንታየሁ ለጥናቱ ገንቢ የሆኑ መረጃዎች በባለሙያዎች መረጃ መሰብሰቡን ገልፀው፤ በጥናቱ የፍላጎት መረጃ መሰረት አዲሱ ገበያ፣ 6ኪሎ፣ 4ኪሎ፣ ቀበና፣ ሃያሁለት፣ ካዛንቺስ እና ቦሌ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙ የብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች መዳረሻ ቦታወች መሆኑ በጥናት ሰነዱ ተመልክቷል።
በተጨማሪም የካ አባዶ፣ ካራ፣ ኮተቤ፣ ጎሮ፣ኮዬ ፍቼ እና ጣፎ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙ የብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች መነሻ ቦታወች መሆናቸው ተገልጿል።
በዋናነትም በውይይቱ ከትራፈክ ማኔጅመንት አንፃር፣ ከመጋጠሚያ ማሻሻያ እንዲሁም ከብዙሃን ትራንስፖርት ስምሪት አንፃር ለትግበራ ገንቢ የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች በተሳታፊዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ የወርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት /WRI/፣ የከተማ አውቶብስ እና የአለም አቀፍ አጋር ድርጅት ባለሙያዎች በውይይቱ ተሳታፊ ሆነዋል።
ቴሌግራም ቻናል:-https://t.me/transport_bureauhttps://
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/aatb
ነፃ የስልክ መስመር 9417 ይጠቀሙ!