የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ፤ግንቦት 12/2016) የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የከተማዋን የትራንስፖርት ስርዓት የተሻለ ለማድረግ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኮሪያ የልማት ድርጅቶች እና በኢትዮጽያ ከኮሪያ አምባሳደር ጋር በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰብያ አዳራሽ ከቀናት በፊት የጋራ ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱም የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር የሚያሻሸሉና በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉ የከተማ ፈጣን አውቶቡስ (BRT) የትራንስፖርት ሰርአቶችን አተገባበር ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
የ BRT መስመር 4 እና የ BRT መስመር 3 የአዋጭነት ጥናት ለማከናወን በተስማማዉ መሰረት ጥናቶቹን ለማከናወን የኮሪያ ኢክስፖርት ኢምፖርት ባንክ (Korea EXIM Bank) እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተገልፆል፡፡
የሁለቱ የፈጣን አውቶብስ መስመሮችም አጠቃላይ እርዝመት 36.5 ኪ.ሜ ገደማ የሚደርስ ሲሆን፤ የ BRT መስመር 4 ከሽሮሜዳ ተነስቶ ለገጣፎ አደባባይ እንዲሁም የ BRT መስመር 3 ደግሞ ከአዲሱ ገበያ ተነስቶ ሃና ማሪያም የሚደርስ መስመር ነው።
ሁለቱ መስመሮች ሙሉ በሙሉ የ Intelligent Transport System (ITS) የሚገጠምላቸና ከተማዋ ለምታስበዉ የስማርት ሲቲ ትግበራ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡
በውይይቱም ላይ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኮሪያ ኢምባሲ፣ የኮሪያ ኢክስፖርት ኢምፖርት ባንክ (Korea EXIM Bank) ፤ Korea International Cooperation Agency (KOICA) ፤ the Korea Foundation for International Healthcare (KOFIH)፣ የጤና ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ቀጣይነት ያላቸው ተመሳሳይ ውይይቶችን ወደፊት ለማከናወነ ስምምነት ላይም ተደርሷል፡፡