በአዲስ አበባ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እያደገ መጥቷል። በከተማችን በሁሉም ደረጃ በበጎነት ተግባራት ላይ የሚሳተፍ ህብረተሰብ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው።
ከአብሮ አደግ ማህበራት እስከ ታላላቅ ድርጅቶች፣ ከመንግስት ሰራተኛ እስከ ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ባህል እያደረገ ይገኛል። የከተማችን ነዋሪዎች በግልና በቡድን በበጎነት ተግባራት ላይ በመሳተፍ በማህበራዊ ችግር ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝና ችግራቸውን ለማቃለል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።
ለአብነት በከተማችን በ2014 ዓ.ም ከግንቦት እስከ ግንቦት ታቅደው በተሰሩ 14 የበጎ ፈቃድና የማህበራዊ ኃላፊነት ፕሮግራሞች 3 ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞችን ማሳተፍ ተችሏል።
በጎ ፈቃደኞች ያወጡትን የጉልበት ፣ የእውቀት ፣ የቁሳቁስና የጊዜ አስተዋፅዖ በገንዘብ ሲተመን 6.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ከግንቦት እስከ ግንቦት በተከናወኑ የበጎነት ተግባራት 1.1 ሚሊዮን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ የከተማችን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በበጎ ፈቃድ በባለሃብቶች አስተዋፅዖ የከተማዋን ገፅታ የሚቀይሩ ቤቶች ተገንብተው ተጠናቀው ለአቅመ ደካሞችና የሐገር ባለውለታዎች ተላልፈዋል።
የአደባባይ ልማቶች ፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታዎች፣ የዳቦና እንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካዎች በአጠቃላይ የህብረተሰቡን ኑሮ የሚቀይሩና የኑሮ ጫናን የሚያቃልሉ የበጎነት ተግባራት ተከናውነዋል።
በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍና ሃብት በማሰባሰብ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ለዜጎች ማዕድ በማጋራት፣ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ ገንዘብ ከፍለው መታከም ለማይችሉ ዜጎች ነፃ የምርመራና የህክምና አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን ችግር ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የተጀመረው ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘንድሮም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን የበጎነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።
በተለይም በክረምቱ ወራት ዝናብ የሚዘንብበት እና ዜጎች ለመኖር ምቹ ባልሆኑ ቤቶች ውስጥ የሚቸገሩበት ወቅት በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ በበጋ ወቅት ሲደረግ የነበረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምት ወቅትም በማስተባበር በሁሉም ክፍለ ከተሞች የአቅመ ደካሞችን ቤት አፍርሶ የማደስ ስራው በይፋ ተጀምሯል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከብን አዳዲስ ችግኞችን የምንተክልበት ወቅት በመሆኑ እስከ 17 ሚሊዩን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል። በማዕድ ማጋራት፤ በትምህርትና ስልጠና፤ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት አገልግሎት፤ በጤናና ቀይ መስቀል ፕሮግራም በአጠቃላይ በ14 ዘርፎች እና በ18 ንፁሳን መርሐ ግብሮች ይተገበራል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፍቃደኝነትን ብቻ የሚጠይቅ፤ በቁርጠኝነትና በሰብዓዊነት ለማህበረሰብ ልማት ብቻ ሲባል በነፃ አገልግሎት የሚሰጥበት ተግባር በመሆኑ የግል ባለሃብቱ፣ ወጣቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሳተፉ ና በሂደቱም የዜግንትና የሰብዓዊነት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይደረጋል፡፡
በጎነት አብሮነታችንን ፣ ወንድማማችነታችንን ፣ ማህበራዊ ትስስራችንን ይበልጥ እያጎለበተው መጥቷል። እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህላችን ዳብሯል። ከመስጠት መቀበል እንዳለ ተረድተን አቅመ ደካሞችን የማገዝ ልማዳችንን ከወትሮው በተለየ ማሳደግ ይኖርብናል።
በመሆኑም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሁሉም ዜጋ ያለማንም አስገዳጅነት ከውስጣቸው በሚሰማቸው ሠብዓዊ አመለካከት ተነስተው ለማህበረሰባቸው ብሎም ለወገናቸው ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልታቸውን፣ እውቀታቸውን በመጠቀም በሁሉም ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥሪውን ያቀርባል።
የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ
አዲስ አበበ ግንቦት 2015