አዲስ አበባ፤ ግንቦት 02፤ 2015 ዓ.ም፤ በከተማዋ የባለ ሶስትና አራት እግር የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ማህበራት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በጎዳና ላይ ቅስቀሳ ለ15 ተከታታይ ቀናት የግንዛቤ መፍጠሪያ ንቅናቄ ተደርጓል፡፡
ቢሮው በቅርቡ የባለ ሶስትና አራት እግር የባጃጅ ትራንስፖርት የአሰራር ስርዓት መመሪያ በማዘጋጀት ወደ አተገባበር መግባቱ የሚታወቅ ሲሆን አገልግሎት አሰጣጡም ቀልጣፋና ሰላማዊ እንዲሆን በባጃጅ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ለሚገኙ ማህበራት በመላ መዲናዋ የግንዛቤ ስራ ተሰርቷል፡፡
በተጨማሪም ከታሪፍ በላይ ባለማስከፈል፣ ከተፈቀደው የመጫን አቅም በላይ ማለትም ከ3 ሰው በላይ ባለመጫን፣ ቢሮው የሚሰጠውን ታሪፍና ታፔላ በመስቀል፣ የታክሲና አውቶቡስ ተርሚናሎች ላይ ባለመቆም እና ተገልጋዮችን ባለማጉላላት አገልግሎት እንዲሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ የጎዳና ላይ ንቅናቄ ተከናውኗል፡፡
በተያያዘም አገልግሎት ሰጪዎቹ በተለይም ከተፈቀደው የባጃጅ መስመር ውጪ አገልግሎት እንዳይሠጡ፤ እንዲሁም የትራንስፖርት ቢሮ መሰል የፀጥታ ተቋማት መረጃ በሚፈልጉበት ጊዜ ተባባሪ በመሆን ሙያዊ ኃላፊነታችውን እንዲወጡም በንቅናቄው ላይ መልእክት ተላልፏል፡፡
ቢሮው ባወጣው መመሪያ መሰረት ማህበራቱ ወደ ተግባር እንዲገቡ የተገለፀ ሲሆን ይህን በማይተገብሩ ህገወጥ አካላት ላይ ተቋሙ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ዘገባው፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ነው
ለበለጠ መረጃ፦ 011 666 33 74 ወይም በነፃ የስልክ መስመር ጥሪ 9417 ይጠቀሙ!