በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማናጅመንት ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የማዕከልና የክ/ከተሞች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በአፈፃፀም መመሪያው የባለ ሶስትና አራት እግር ተሽከርካሪ ወይም ባጃጅ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ካሁን ቀደም ሲያጋጥሙ የነበሩ የሕግ ጥሰቶችንና የደንብ መተላለፎችን ለመከላከል ሲባል አገልግሎት ሰጪዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ፣ የአዲስ አበባ የሠሌዳ ቁጥር እንዲሁም በማህበር መደራጀት እንደሚኖርባቸው ተገልጿል።
በመድረኩም በአዲስ አበባ፣ የከተማ አስተዳደሩን ታርጋ ለጥፈውና የአዲስ አበባ መታወቂያ ይዘው ከሚሰሩት ይልቅ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ አሽከርካሪዎች መበራከት የፀጥታ ችግር ሆነው ቆይተዋል ተብሏል።
ይህ ደግሞ በተለይም በወንጀል ድርጊት ላይ ተሳትፈው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ጭምር አዳጋች እንደነበር ተገልጿል።
የባጃጅ ትራንስፖርት የከተማዋን ዘመናዊ እሳቤ የሚመጥን ስላልሆነ በሂደት መሉ በሙሉ አገልግሎቱ የሚቋረጥ ቢሆንም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን የባለሶስት እግር አሽከርካሪዎች የአዲስ አበባ መታወቂያ፣ ታርጋና በማህበር መደራጀት ይኖርባቸዋል ተብሏል።
ነገር ግን አሁን ላይ በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ሰፊ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎ ፍላጎት በመኖሩ በነዚህ አካባቢ ያለው ፍላጎት በሌላ አማራጮች እስኪተካ ድረስ አገልግሎቱ ይቀጥላል ብሏል።
ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአገልግሎት ዘርፉ ከፀጥታ ስጋት ነፃ ሆኖ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ደረጃ በደረጃ ሕጋዊ አሠራሮች ይተገበራሉ፣ የፀጥታ መዋቅሩም ለአፈፃፀሙ ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ይሠራል ብለዋል።
@ አዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ