በአዲስ አበባ ከተማ በየእለቱ 1 ሺህ አውቶቡሶች በ172 መስመሮች ተሰማርተው ከ1 ሚሊዮን በላይ የከተማዋን ነዋሪ እያገለገሉ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ዓለሙ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር እንደገለጹት አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት እና ሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት ከተዋሃዱ በኋላ በቀን የሚሰማሩት አውቶብሶች ቁጥር ከ700 ወደ 1 ሺህ ከፍ ብለዋል።
ድርጅቱ በውስጥ አቅምና ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር አሰራሩን በማዘመን ቁጥጥሮችን በቴክሎኖጂ በመታገዝ ማከናወን እንደጀመረም ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አውቶቡሶች በየፌርማታዎች ስንት ሰዓት እንደሚመጡ ለተሳፋሪዎች መረጃ የሚገልጹ ዲጂታል ሰሌዳዎችን የመትከል ሥራ እንደተጀመረም ነው ሥራ አስኪያጁ የገለፁት።
ድርጅቱ አምስት ዴፖዎች (የአውቶብስ ማሳደሪያ ስፍራዎች) ያሉት ሲሆን ከነዚህ ዴፖዎች በቀን 1 ሺህ 100 አውቶቡሶች የሚያቀርብ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ እስከ 1 ሺህ የሚሆኑት ስምሪት ላይ እንደሚሆኑም ነው የተጠቆመው።
የአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ከጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅትን እና ሸገር ብዙሃን ትራንስፖርትን በመዋሃድ የተፈጠረ ድርጅት እንደሆነ ይታወቃል።
ከውህደቱ በኃላ ከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ አውቶቡሶችን በመግዛትና ተበላሽተው ቆመው የነበሩ አውቶብሶችን በመጠገን ወደ ሥራ በማስገባት ተደራሽነቱን እንዳሰፋ አቶ ግዛው አብራርተዋል።
ኢቢሲ ሳይበር በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የተገልጋይ አስተያየቶችን የተቀበለ ሲሆን አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች በአውቶቡሶቹ አገልግሎት ደስተኛ ሲሆኑ ከመርካቶ፣ ከአውቶቡስ ተራ እና ከመገናኛ ወደ አየር ጤና የሚሄዱ ተገልጋዮች ግን አውቶቡስ እስከ 1 ሰዓት ድረስ እንደሚያስጠብቃቸው ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ለ80 ዓመት ያህል ያገለገለው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅትን ከሸገር ባስ ጋር ማዋሃዱ ይህን ታሪካዊ ድርጅት ከማቆየት አንጻር ስጋት አይኖረውም ወይ ብለን ላቀረብነው ጥያቄ፤ የተዋሃደው አስተዳደራቸው እንጂ ብራንዳቸው አንዳልሆነ እና አውቶቡሶቹ አሁንም በቀድሞ ስያሜያቸው እንደሚጠሩ ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ዘገባው፦የኢቢሲ ነው