[:en]የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በማስቀጠል በትራንስፖርት ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በዘርፉ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች አስታወቁ፡፡
የክልልና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አመራሮች በተገኙበት በአዳማ ከተማ በተካሄደው የሶስት ቀናት ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ላይ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ቅንጅታዊ አሰራሩን በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ለማድረግ ከዚህ ቀደም የነበረውን አደረጃጀት በመፈተሽ በፌደራል፣ በክልልና በከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ በባህሪው የተለያዩ አካላት የሚሳተፉበት፣ ከፍተኛ ሀብት የሚፈልግ፣ ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ ዘርፉን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም የክልሎችና የከተማ አስተዳደር አካላት ተሳትፎን በማሳደግ ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት የተናገሩት ተሳታፊዎች በተለይ የታዳጊ ክልሎችን አቅም ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
በዚሁም መሰረት በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ፣ በታሪፍ፣ በአውቶቡስ ደረጃዎች እና በመናኸሪያ ስታንዳርድ ላይ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በጋራ የሚተዳደሩበት መመሪያ መውጣቱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
በመንገድ ደህንነት በ2010 በጀት ዓመት በተሰራው ስራ በአንዳንድ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የትራፊክ አደጋ መቀነስ እንደተቻለ ከቤቱ ተገልጾ አደጋውን ቀጣይነት ባለው መንገድ ለመቀነስ የትራፊክ ቁጥጥር አሰራርን የማጎልበት፣ የኢንጂነሪግ አሰራርን የማሳደግ እና የክትትልና ቁጥጥር አግባቦችን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ መሰራት እንዳለበት በውይይቱ ተነስቷል፡፡
ሀገር አቀፍ የምክክር መድረኩን በይፋ መከፈትን አስመልክቶ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣና ዋና ዳይሬክተር ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ እንደተናገሩት ለብዙ ዓመታት በአግባቡ ላልተመለሱ የትራንስፖርት ዘርፍ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በተለይ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በተሽከርካሪ ምርመራ ሂደት ለሚታዩ የስነ ምግባር ጉድለቶች እና በህዝብ ዘንድ ቅሬት በሚፈጥሩ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ርብርብ ለማድረግ የዘርፉ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚጠናከርም ተናግረዋል፡፡
በተለይ ትክክለኛውን የአሰለጣጠን ሂደት ተከትለው መንጃ ፈቃድ በማይሰጡ አካላት ላይ ተገቢው የክትትል ስርዓት እንደሚዘረጋ የተናገሩት አቶ አብዲሳ ችግሩ በሚታይባቸው ተቋማት አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል፡፡
በትራንስፖርት ዘርፍ ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ ከምንጊዜው በላይ ዝግጅት መደረጉን ዋና ዳይክተሩ አስታውቀዋል፡፡
በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ወልደዮሃንስ በበኩላቸው የትራንስፖርት ዘርፍ መዘመን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሳለጥ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ በመኖሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደስራ ለማስገባት የዘርፉ ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተር አያይዘውም የዘርፉ ተቀዳሚ ዓላማ ለህብረተሰቡ ግልጋሎት መስጠት መሆኑን ገልጸው ተቋማት አዳዲስ አሰራሮችን ወደስራ ከማስገባታቸው በፊት ከዕቅድ ጀምሮ በእያንዳንዱ ትግበራዎች የቅርብ ግንኙነትና ምክክር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀናት በተዘጋጀው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ በ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም፣ በ2011 በጀት ዓመት የቢኤስሲ እቅድ፣ በፌደራል፣ በክልልና በከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮዎች ቅንጅታዊ አሰራር እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ጥናቶች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ዘገባው፦ በትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው
ለበለጠ መረጃ፦ 011 557 32 66