አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2012፤ በበጀት ዓመቱ የስምንት ወራት በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርት ቢሮ በ2012 በጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ከተጠሪ ተቋማት ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አድርጓል፡፡
በከተማዋ የትራንስፖርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት አዳዲስ የስምሪት መስመሮች መጀመራቸው ተገልጾ አንበሳ የከተማ አውቶቡስን ወደ 125 እና ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርትን ወደ 52 መስመሮች ማሳደግ ተችሏል፡፡
የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ስምሪትንና ፍሰትን ለማሻሻል 100 ተጨማሪ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ወደስራ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፥ መስመር የማራዘምና ታሪፍ የማሻሻል ስራም ተሰርቷል፡፡
በመዲናዋ 10 ሺህ ታክሲ ባለንብረቶችን በ181 ማህበራት በማደራጀት እየሰጡ የሚገኘው አገልግሎት መሻሻል ታይቶበታል፡፡
ከስምሪትና ትርፍ ከመጫን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል “አዲስ ጉዞ” ሶፍትዌር የሙከራ ትግበራ መጀመሩም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ስጦታው አካለ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት “አዲስ አበባ ከእርምጃ ወደ ሩጫ” በሚል የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥና የትራፊክ ፍሰት የሚያሻሽሉ ተግባራት በቀጣይ ሁለት ወራት ይከናወናሉ፡፡
ከስምሪት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የክትትልና ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
የህዝብ መጉላላትን ለማስቀረት የብዙሃን ትራንስፖርት አማራጮችን ከነበረዉ የማስፋትና ድግግሞሽን የመጨመር ስራ እንደሚሰራም አቶ ስጦታው አስታውቀዋል፡፡
በመጨረሻም በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት ተደርጎ አስተያየት የተሰጠባቸው ሲሆን፥ ጠንካራና ደካማ ጎኖችንም በመለየት ቀጣይ አቅጣጫዎችንም በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡