የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ዣንጥራር አባይ የቃሊቲን የትራፊክ ኮምፕሌክስ ማሰልጠኛ ግቢ የሌማት ትሩፋት እና የአረንጓዴ ልማት ስራን በይፋ አስጀመሩ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ አስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የ90 እና 60 ቀናት እቅድ በማቀድ በርካታ ተግባራትን በእቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑንና ከተያዙ እቅዶችም መካከል አንዱ የአቃቂ ማሰልጠኛ ተቋም የአረንጎዴ ልማት ግንባታ መሆኑንና ቦታውን አረንጓዴ በማድረግ የሀብት ምንጭና የስራ እድል መፍጠር እንደሚቻል አቶ ዣንጥራር አባይ ገልፀዋል።
የፌደራል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳንጌ ቦሩ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት በትራፊክ አደጋ የሚደረስን ጉዳት ተከላክሎ የሚያሽከረክር ብቃት ያለው አሽከርካሪ ማፍራት እንደሚጠብቅባቸውና ከልማት ቱሩፋቱ በተጨማሪም ሌሎች ባለሀብቶችን በማስተባበር የከተማን ግብርና የምንተገብርበት ተቋም ለማድረግ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት በመርሀ ግብሩ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ
የቃሊቲ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም በቀን ከአራት ሺህ በላይ ተገልጋዮችንና ከአራት መቶ በላይ የተቋሙ ባለሙያዎችን ማስተናገድ የሚችል ትልቅ ተቋም ቢሆንም ቦታው ለደንበኞች ንፁህና ምቹ ማረፊያና በቂ መፀዳጀ የሌለው በመሆኑ ቦታውን በማልማት አረንጓዴ ማድረግ አስፈልጎል ብለዋል::
የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋም ተወካይ አቶ አምሳሉ አምባው ማሰልጠኛው እየሰጠ ያለው አገልግሎት የሚመጥን ውብ፣ ማራኪና አረንጓዴ በማድረግ በ6.5 ሚሊየን ብር የአረንጓዴ የሌማት ቱሩፋትና የአረንጓዴ ልማት ስራን ጀምረው እንደሚያጠናቅቁ ቃል በመግባት፤ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች ተሳትፎ በማድረግ ሀገራዊ ግዴታቸውን ሲወጡ እንደነበረ አስታውሰዋል።
በመጨረሻም በአረንጓዴ ልማት ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚ፣ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትና የቃሊቲ ማሰልጠኞ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሀ ግብሩ ተሳታፊ ሆነዋል።