አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22፤ 2015 ዓ.ም፤ በመዲናዋ ከ208 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት የትራፊክ ፍሰት የሚያሳልጡና የመንገድ ደህንነት ለማሻሻል የሚረዱ 26 መጋጠሚያዎችን እና አደባባዮችን የምህንድስና ማሻሻያ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገለፀ፡፡
በከተማችን የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎችን እና በፍሰቱ መጨናነቅ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ካላቸው ቦታዎች መካከል አደባባዮችና መጋጠሚያዎች ከፍተኛ ሚና ስላላቸው ቦታዎቹ ተመርጠው የማሻሻያ ስራ መጀመሩን ተመላክቷል፡፡
የተመረጡ መጋጠሚያዎች እና አደባባዮችም ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የማሻሻያ ስራዎች እየተሰራ ሲሆን ዛሬ የዘርፉ አመራሮች እና ሠራተኞች የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
ከ26 መጋጠሚያዎች እና አደባባዮች መካከልም 4ቱ ማለትም ሳሪስ ሃና 58 ቁጥር ማዞሪያ፣ ቦሌ መድሃያለም አካባቢ፣ አፍንጮ በር ናይጀሪያ ኤምባሲ እና ቤቴል ቀራኒዮ 40 ሜትር መንገድ አካባቢ ያለው አደባባይ የማሻሻያ ስራው ያለበትን ሁኔታ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እና የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አመራሮች ጎብኝተዋል፡፡
ማሻሻያዎቹ የእግረኞቹን ደህንነት የሚያረጋግጡ እና የተሸከርካሪን ፍሰት የሚያሳልጡ ሲሆን አራት ቅድሚያ የተሰጣቸው ቦታዎች ስራቸው ተጠናቋል፡፡
በመጋጠሚያዎቹ ላይ የሚደረገው ማሻሻያ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ባደረገው ጥናት፣ ከትራፊክ ፖሊሶች እና ከህብረተሰቡ በተገኙ ሀሳቦች ግብዓትነት በመነሳት መሆኑ የተመላከተ ሲሆን ስራዎቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ በአካባቢዎቹ የሚስተዋለውን የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ እና የትራፊክ ግጭቶችን ለመቀነስ የጎላ ሚና እንዳላቸውም ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡