ከከተማው አስተዳደር ግዙፍ የልማት ግንባታዎች መካከል፣ ሾላ ገበያ አካባቢ በመሬት ውስጥ እየተገነባ የሚገኘው የየካ ቁጥር ሁለት የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠቃሽ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደቦ ቱንካ እንዳስታወቁት፤ በመሬት ውስጥ የሚሰራው የየካ ቁጥር ሁለት የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት የነበሩበትን በርካታ ተግዳሮቶች በመቅረፍ፤ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በ 7,247 ካሬ ላይ ያረፈው የመኪና ማቆሚያው ግንባታ ሲጠናቀቅ፤ ከዘጠኝ መቶ መኪና በላይ የመኪና ማቆሚያ ቦታ በማቅረብ፤ በሾላ ገበያ አካባቢ ያለውን የመኪና ማቆሚያ የቦታ እጥረት በመቅረፍ፤ የአካባቢውን የትራፊክ ፍሰት ያሳልጣል።
በከተማው ለሚስተዋለው የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ ምክንያት፣ የመንገድ ዳርን ለመኪና ማቆሚያነት መጠቀም፤ ለትራፊክ ፍሰት መስተጓጎል እንደ አንድ ተግዳሮት እየሆነ ይገኛል፡፡ ይህን መሰል ችግር ለመቅረፍና የተሽከርካሪ ደህንነትን ለመጠበቅ፤ ቀደም ሲል በሜጋ ፕሮጀክቶች የተገነቡትን ጨምሮ አሁንም በመገንባት ላይ ያሉት የመኪና ማቆሚያ (Parking) ግንባታ ስራዎች፣ ለከተማችን የትራፊክ ፍሰት ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡