በሐምሌ ወር በ1,353 የህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ፡፡
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17፤ 2014፤ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ባደረገው ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት በሐምሌ ወር በተሽከርካሪያቸው ታሪፍ ባለጠፉ 1,353 ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የቢሮው ትራንስፖርት አገልግሎት ክትትልና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡
ቢሮው እርምጃውን የወሰደው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሻሻል ከተቋቋመው ግብረ ሀይል ከትራፊክ ፖሊስ፣ ከፀጥታ አካላት፣ ከክፍለ ከተማ ሰላምና ደህንነት፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ እና ደንብ ማስከበር እንዲሁም ከአስራ አንዱም ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሠራተኞችና አመራሮች ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን በመፍጠር መሆኑን አቶ ዬሴፍ ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ የቢሮውን ህጋዊ ማህተም ያረፈበትን የታሪፍ ዝርዝር ወረቀት በመመልከት ብቻ ታሪፉን መክፈል እንዳለበትና ታሪፍ ያልሰቀሉ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የተጠየቁትን ታሪፍ መክፈል እንደሌለባቸውና፤ በአንዳንድ አከባቢዎች ህብረተሰቡ መብቱን ለማስከበር እያደረገ ያለው ተግባር አበረታችና የሚመሰገን ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ታሪፍ ወረቀት ለተገልጋዩ በማይታይ መልኩ ያልሰቀሉ፣ የታሪፍ ወረቀቱን ከዕይታ ውጪ የሚያስቀምጡ፣ ህብረተሰቡን ታሪፍ ተቀይሯል አሁን ያለው ታሪፍ ወቅታዊ አይደለም ወዘተ ብለው መረጃ ለህብረተሰቡ የሚሰጡ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከዚህ ህገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሃላፊው አሳስበዋል፡፡
ዘገባው፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው፡፡
ነፃ ስልክ ፡-9417 ይደውሉ
የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-