የልደታ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት
(የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሚያዚያ 9/2016ዓ.ም) የልደታ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅሀፈት ቤት የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸሙንና የ100 ቀናት እቅድ ከአጠቃላይ ሰራተኞችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ገምግሟል፡፡
የልደታ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ይብጌታ ሽኩር በከተማ ደረጃ ሪፎርም ከተደረጉ ተቋማት መካከል ቢሮው አንዱ መሆኑን ገልፀው፤ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በቀሪ የ100 ቀን እቅድ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚጠበቅበትና ሁሉም የትራንስፖርት ዘርፍ አካላት በህዝብ አገልጋይነት መንፈስ በአገልግሎታችን የሚረካ ተገልጋይ ለመፍጠር መስራት እንደሚገባ በአንክሮ ገልፀዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ከሙያዊ ስነምግባር ውጪ አገልግሎት የሚሰጡ የቢሮውና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል፡፡
ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በ9 ወራት 13,211 አጥፊ አሽከርካሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን፣ በቀጣይም ለህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ምንጭ የሆኑ ቦታዎችን በጥናት በመለየት እንደሚሰራና ለአብነትም ከሞላ ማሩ እስከ ተክለሀይማኖት ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት መታቀዱን በውይይቱ ተገልፆል፡፡
በመጨረሻም የውይይቱ ተሳታፊዎች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በ9 ወራት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሰራው ስራ አበረታች መሆኑን ገልፀው፤ ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡