የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል እየታየበት ቢሆንም የበለጠ ሊሰራበት እንደሚገባ ተገለፀ

የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል እየታየበት ቢሆንም የበለጠ ሊሰራበት እንደሚገባ ተገለፀ

በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ መጠነኛ መሻሻሎች እየታዩበት ቢሆንም የበለጠ ሊሰራበት እንደሚገባ ተገልጋዮች ገልፀዋል፡፡

በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ቢሮው ግብረ-ሃይል በማቋቋም አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

የቢሮው ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አዲሱ ገበያ የትራንስፖርት ተርሚናል በመገኘት ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ቅኝት አድረጓል፡፡

በምልከታውም የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎችን እና የጉለሌ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጁን በማነጋገር  ዘገባ አዘጋጅቷል፡፡

ተገልጋይ አቶ ተሾመ ታደሰ እንደነገሩን የትራንስፖርት መጫኛና መውረጃ ተርሚናል የመቀየር ስራ ለአገልግሎቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በነባሩ ተርሚናል ሰልፍ ከሰልፍ በመደራረብ እና በመጨናነቁ የተነሳ ትርምስ ይስተዋል እንደነበር ያወሱት አቶ ተሾመ የትራንስፖርት አገልግሎቱ መጠነኛ መሻሻል መታየቱን ገልፀዋል፡፡

በትራንስፖርት ሰልፍ ላይ ከርስ በርስ መገፋፋት ውጭ በሆነ መንገድ አገልግሎቱን ለማግኘት ስርዓት የማስከበሩ ሂደት እንዲጠናከርም ሃሳባቸውን ሰንዝርዋል፡፡

አያይዘውም ተገልጋይ አቶ ተሾመ እንደተናገሩት መሻሻሎቹ ቀጣይነት እንዲኖራቸው በትኩረት መሰራት እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡

ወ/ሮ መስከረም ተካ በበኩላቸው  ሰሞኑን የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል ታይቶበት የነበረ ቢሆንም አሁንም ችግሮች እንዳሉ ገልፀዋል፡፡

በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት ችግር እና የመንገድ መጨናነቅ እንደሚስተዋልም ተናግረዋል፡፡

በተለይ የተማሪዎች መግቢያና መውጫ ሠዓት ላይ የትራንስፖርት ረዣዥም ሰልፎች እንደሚስተዋልም ወ/ሮ መስከረም አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ተስፋዬ  እንዳስታወቁት በክፍለ ከተማው የሚታዩ የትራንስፖርት ችግሮችን ከቢሮውና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የሚታዩ ችግሮችን በመለየት አፋጣኝ መፍትሔዎችን ለአብነት የተርሚናል ቦታዎች ቅየራ፣ ህገ-ወጥ ተርሚናሎችን ማስቀረት እና ሌሎች የማስተካከያ ርምጃዎች መወሰዳቸውን አቶ ሳሙኤል ገልፀዋል፡፡

ነባር ተርሚናሎቹ መብራት አቅራቢያ በመሆናቸው ለፍሰቱ ችግር እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ሳሙኤል ክፍት ቦታዎችን በመፈለግ ለአገልግሎቱ ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ስራው መከናወኑንም አስታውቀዋል፡፡

የተቀየሩ የትራንስፖርት መጫኛ ተርሚናሎቹ የመንገድ መጨናነቅ ይፈጠር የነበረውን ሁኔታ ማስተንፈስ ማስቻሉንም ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ መሻሻሎች እየታዩበት መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ አንዳንዴ የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ከሰሞኑ የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ የትራንስፖርት አቅርቦት ችግር ቢኖርም የተመደቡ ተሽከርካሪዎችን በሙሉ አቅም እንዲሰሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ 

በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍና አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ ቢሮው የሱፐርቪዥንና ድጋፍ ቡድን በማቋቋም ከጥቅምት 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር መገባቱ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply