በሶስት ዓመታት ብቻ በትራንስፖርት መሰረተ- ልማት ሀብቶች በደረሰ ስርቆት ከ35 ሚሊየን በላይ ኪሳራ መድረሱ ተገለፀ

በሶስት ዓመታት ብቻ በትራንስፖርት መሰረተ- ልማት ሀብቶች በደረሰ ስርቆት ከ35 ሚሊየን በላይ ኪሳራ መድረሱ ተገለፀ

በሶስት ዓመታት ብቻ በትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ሀብቶች በደረሰ ስርቆት ከ35 ሚሊየን በላይ ብር ኪሳራ መድረሱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ገለፀ፡፡

በመዲናዋ ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም በትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ሀብቶች በተለይ በመንገድ መብራቶች፣ የማንሆል ክዳኖች እና የአውቶቡስ መጠበቂያ መጠለያዎች ላይ በደረሰ ስርቆት ከ35 ሚሊየን በላይ ኪሳራ ደርሷል፡፡

ቢሮው የትራንስፖርት መሠረተ-ልማት ሀብቶችን ከብክነት ለመታደግና በተቀናጀ መንገድ ለማስተዳደር ያለመ ጥናት ቀርቦ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱ የትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ እንደተናገሩት በመዲናዋ የሚታዩ የትራንስፖርት መሠረተ-ልማት ሀብቶችን ከብክነት ለመታደግ ጥናቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው አያይዘውም አንዱ ተቋም የሰራውን መሰረተ-ልማት ሌላው ተቋም የሚያፈርስበት ሳይሆን የተቀናጅ አሰራር በመዘርጋት ሀብቶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በተለይ የትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ሀብቶች በስርቆት እና በህገ-ወጥ ማስታወቂያዎች የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመታደግ ሀብቱን የሚያስተዳድሩ ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ምክትል ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

በቢሮው የትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ሀብቶች አስተዳደር ቡድን መሪ ወ/ሮ ካሳዬ እምሬ በበኩላቸው በስርቆት ምክንያት በትራንስፖርት መሰረተ ልማት ሀብቶች ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በመዲናዋ መሰረተ-ልማቶቹ በሚደርስ ስርቆት ሀብቶቹ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የትራንስፖርት መሠረተ-ልማት ሀብቶች በተቀናጀ እና በዘመናዊ ሁኔታ ማስተዳደር ስላልተቻለ አንዱ የሰራዉን ሌላዉ ሲያፈርስ በርካታ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ሲባክን እንደነበር አንስተዋል፡፡

በከተማችን እየለሙ ያሉትን የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ረጅም የአገልግሎት ዘመን እንዲኖራቸዉ ሁሉም ተቋማት ተናበውና ተቀናጅተው መስራት አለባቸው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

Leave a Reply