ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቁ በካይ ጋዞች በከባቢ አየር ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12፤ 2015 ዓ.ም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የሞተር አልባ ትራንስፖርት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት የትራንስፖርት ዘርፍ የአየር ንብረት ለውጥ ቡድን ከከተማው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በጋራ በመሆን በከባቢ አየር ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ በተመለከተ ዘርፉ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ስልጠና ሰጠ፡፡

የትራንስፖርት ቢሮው ዓላማ ከተፈጥሮ አካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ሲሆን ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የአየር ንብረት ለውጥ ምንነት፣ መንስዔ፣ ተፅእኖ እና የመፍትሔ እርምጃዎችን በሚመለከተው ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ስልጠናው በዋናነት ከትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሚለቀቁ በካይ ጋዞች በከባቢ አየር ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ በመረዳትና በመገንዘብ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ያስችላል፡፡

በተጨማሪም አቅም ማጎልበቻው ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ፣ የብዝሀ ህይወትን በመንከባከብና በመጠበቅ፣ የከባቢ አየር ብክለትን መቋቋም የሚችሉ እፅዋትን በብዛት በመትከል ሀገራችን ብሎም ከተማችን ከሚደርስባት ከባቢያዊ የአየር ብክለት ለመታደግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ተብሏል፡፡

በዚህ ረገድ ቢሮው አካባቢያዊ ተስማነቱ የተረጋገጠ የትራንስፖርት ስርዓት ለመፍጠር በፍኖተ-ካርታው እና በራዕዩ ላይ አስቀምጦ የብዙሃን እና ሞተር አልባ ትራንስፖርትን በከተማዋ ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

በውይይቱም የ16ቱም የትራንስፖርት ማህበራት ተወካዮች፣ የትራንስፖርት ቢሮ ሴክተር ተቋማት፣ የቢሮው ዳይሪክተሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለሙያዎች፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በድምሩ 38 ሙያተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ዘገባው፡-በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው፡፡

ለበለጠ መረጃ፡- 011-666-3374 ወይም ነፃ የስልክ መስመር 9417 ይጠቀሙ!

Leave a Reply