አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ከባለ ሶስትና አራት እግር ባጃጅ ባለንብረቶች ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ አተገባበር ዙሪያ ውይይት ማካሄድ ጀመሩ፡፡

አዲስ አበባ፤ ህዳር 13፤ 2015 ዓ/ም፤ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮልፌ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ከባለ ሶስትና አራት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ አተገባበር ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ ማካሄድ ጀመረ::

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮልፌ ቀራኒዮ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጁ አቶ ጀማል ሰፋ በከተማችን አዲስ አበባ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የባለሶስትና አራት እግር የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በህብረት ስራ በመደራጀት በዘርፉ ፈቃድ ሲሰጥ የነበረ የትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓት በአሰራር መመሪያ በመደገፍ አገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል ቢሮው እየሰራ መሆኑን በመግለፅ፤ ቢሮው እያዘጋጀ ያለውን መመሪያ ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት የጋራ ውይይት ማድረግ በማስፈለጉ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቀሪ ሰባት (7) የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችም ውይይቱ የሚካሄድ ይሆናል ብለዋል፡፡

በውይይቱም በከተማዋ አዲስ አበባ የባለሶስትና አራት እግር (ባጃጅ) ተሽከርካሪዎች ለትራፊክ ፍሰት መስተጓጎልና አደጋ መንስኤ መሆናቸው፣ ከመጫን አቅም በላይ ሹፌርን ጨምሮ እስከ 6 ሰው መጫን፣ የአገልጋይነት መንፈስ አለመኖር፣ የተቀመጠ ታሪፍ ባለመኖሩ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ማስከፈል ፣ የስምሪት መስመር መቆራረጥ፣ በተሽከርካሪዎቹ ህገወጥ ተግባራት እየተስፋፋ መምጣቱ፣ አባል ያልሆነ በተደራጁ የባጃጅ ማህበራት ላይ ለመግባት ከህግ ውጭ ከፍተኛ መጠን ያለው ክፍያ መጠየቁ፣ ከደረጃ በታችና በላይ እንዲሁም ያለ መንጃ ፍቃድ ማሽከርከርና ለከተማዋ ለሰላምና ፀጥታ ስጋት መሆኑ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡

የባለሶስትና አራት እግር (ባጃጅ) ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች በውይይቱ የተነሱ ችግሮች ትክክል መሆኑን በመግለፅ፤ መንግስት የነዳጅ ድጎማ እንዲያደርግላቸውና የአገልግሎት ታሪፋ አዋጪ እንዲሆን ፣ በህጋዊ መልኩ ተደራጅተው አገልግሎት ለመስጠት ትራንስፖርት ቢሮና ሌሎች የመንግስት አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደረግላቸው በመጠየቅ ቢሮው ባዘጋጀው የአሰራር መመሪያ ለመስራትና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል::

የኮልፊ ቀራኒዮ ክ/ከተማ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሺነር ሞቱማ ቲማ የትራንስፖርት ቢሮ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና የህግ አስከባሪ አካላት ህግን ለማስከበር መረጃ ሲጠይቁ ተባባሪ መሆን እንደሚገባ ጠቁመው ፤ ለፀጥታ ችግር የሚሆኑ ጉዳዮችን በመፍታት ለሚወጣው መመሪያ ተገዢ መሆን እንደሚገባ በአፅንዖት ገልፀዋል።

በመጨረሻም በውይይቱ ከ ሁለት ሺህ አምስት መቶ (2500) በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ የኮልፊ ቀራኒዮ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት፣ የኮልፊ ቀራኒዮ ፖሊስ መምሪያ ፣ የክፍለ ከተማው ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምዕራብ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ፣ የክፍለ ከተማው የትራፊክ ፖሊስ መምሪያ፣ በክፍለ ከተማው የሚገኙ የባለሶስትና አራት እግር ባጃጅ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች፣ ደንብ ማስከበር ፅህፈት ቤት እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Leave a Reply