በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የባለሶስትና አራት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች የአሰራር መመሪያ ሊዘጋጅላቸው መሆኑ ተገለፀ፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተሰማርተው አገልግሎት እየሰጡ ካሉ የባለሶስት እና አራት እግር የባጃጅ ተሽከርካሪ ማህበራት ተወካዮች ጋር አገልግሎቱን በስርዓትና በመመሪያ ለመምራት የሚያስችል የጋራ ውይይይት አደረጉ፡፡

በከተማችን አዲስ አበባ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የባለሶስትና አራት እግር የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በህብረት ስራ በመደራጀት በዘፍቃድ ሲሰጥ የነበረ የትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓት በአሰራር መመሪያ በመደገፍ አገልግልት አሰጣጡ እንዲሻሻል ቢሮው እንደሚሰራ አሳውቋል፡፡

በውይይቱም በከተማዋ አዲስ አበባ የባለሶስትና አራት እግር (ባጃጅ) ተሸከርካሪዎች ለትራፊክ ፍሰት መስተጓጎልና አደጋ መንስኤ መሆናቸው፣ ከመጫን አቅም በላይ ሹፌርን ጨምሮ እስከ 6 ሰው መጫን፣ የአገልጋይነት መንፈስ አለመኖር፣ የተቀመጠ ታሪፍ ባለመኖሩ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ማስከፈል ፣ የስምሪት መስመር መቆራረጥ፣ በተሽከርካሪዎቹ ህገወጥ ተግባራት እየተስፋፋ መምጣቱ፣ አባል ያልሆነ በተደራጁ የባጃጅ ማህበራት ላይ ለመግባት ከህግ ውጭ ከፍተኛ መጠን ያለው ክፍያ መጠየቁ፣ ከደረጃ በታችና በላይ እንዲሁም ያለ መንጃ ፍቃድ ማሽከርከርና ለከተማዋ ለሰላምና ፀጥታ ስጋት መሆኑ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡

የባለሶስትና አራት እግር (ባጃጅ) ማህበራት ተወካዮች በውይይቱ የተነሱ ችግሮች ትክክል መሆኑን በመግለፅ፤ ከአደረጃጀትና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያዘ እየተፈጠረው ያለውን ችግር በቀጣይና በዘላቂነት ለመፍታት ትራንስፖርት ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ በሚያወጣው የአሰራር መመሪያ ለመስራትና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ፖሊሲ ከተማዋን የሚመጥን ዘመናዊ የብዙሀን ትራንስፖርት አገልግሎትን ማስፋት እንደሆነ በመግለፅ፤ ነገር ግን አሁን ባለን የትራንስፖርት ፍላጎት መነሻነት የባለሶስትና አራት እግር (ባጃጅ) ተሸከርካሪዎች በቀጣይ ቢሮው በሚያስቀምጠውና በሚፈቅደው መመሪያና የስራ አቅጣጫ በታፔላ፣ የትራፊክ መጨናነቅ በማይኖርበት፣የትራንስፖርት አቅርቦት ባልተስፋፋበት፣በተመረጡ የጉዞ መስመሮች ላይ በስምሪት መስመርና ኪሎ ሜትርን መነሻ በሚያደርግ ህጋዊ የታሪፍ ተመን አገልግሎት እንዲሰጡ የአሰራር መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ተግባር ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የባለሶስትና አራት እግር ተሸከርካሪዎች አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ትልቅ የከተማዋ ስጋት መሆናቸውንና ትራንስፖርት ቢሮ በቀጣይ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ችግሮቹ የሚፈቱ ሲሆን ይህ እስከሚፈፀም ህግና ደንብን አክብረው መስራት እንደሚገባቸውና ይህንን በማይፈፅሙት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ህጋዊና የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የስራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ መመሪያ፣ የባለሶስትና አራት እግር ባጃጅ ባለንብረት ማህበራት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በውይይቱ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Leave a Reply