በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ምክር ቤት የ2015 በጀት ዓመት የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫውን ገመገመ።

(ሚያዚያ 17/2015 ዓ.ም)፡ – የአዲስ አበባ መንገድ ደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ የትራፊክ አደጋ አስከፊነት በመግለፅ፤ በ2015 በጀት ዓመት ስድስት ወራት 211 ሰዎች በመንገድ ትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ፤991 ከባድ እና 749 ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ገልፀዋል።

ችግሩንም ለመፍታት በከተማ አስተዳደሩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ምትኩ በተለይም የ 13 ዓመት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በመንደፍ በከንቲባ ደረጃ የሚመራ ምክር ቤት በማቋቋም የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እና የመንገድ ደህንነት ምክር ቤቱ ጸሃፊ አቶ ክበበው ሚደቅሳ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አባል ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በግማሽ ዓመቱ የተተገበሩ ዋና ዋና ተግባራትን፣ በስራ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ እርምጃዎችንና የቀጣይ የምክር ቤቱ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትና ተሳታፈዎችም በመንገድ ደህንነት ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም በቀጣይ መሰረት የሚገባቸው ያሎቸውን ጉዳዮች ያነሱ ሲሆን በዋናነትም ቅንጅታዊ አስራርን ማጠናከር፣ ወቅታዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በተለያዩ ዘዴዎች ለህብረተሰቡ ማቅረብ፣ የፍጥት መገደቢያ ጉብታዎች በስታንዳርዳቸው ቢሰሩ የሚሉ ሀሳቦች ተነስተዋል።

በመጨረሻም የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ለተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚተው ሳይሆን ከምን ጊዜውም በላይ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እና ቅንጅታዊ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑ፣ የምክር ቤት አባል ተቋማት ተሳትፎ የማይተካ ሚና እንዳለውና የመንገድ ደህንነት የስትራቴጂ ዕቅዱ ስኬታማ እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል ።

በጉባኤውም የምክር ቤት አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ አርቲስቶች፣ የነዋሪዎች ፎረም ተወካዮች፣ የሚዲያ አካላት፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

Leave a Reply