በታክሲዎችና ብዙሃን ትራንስፖርት የተሳፋሪ ቁጥር በግማሽ እንዲቀንስ ውሳኔ ተላለፈ፡፡

በታክሲዎችና ብዙሃን ትራንስፖርት የተሳፋሪ ቁጥር በግማሽ እንዲቀንስ ውሳኔ ተላለፈ፡፡

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2012፡ የትራንስፖርት ቢሮ በታክሲዎችና ብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን ዙሪያ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች የተሳፋሪ ቁጥርን በግማሽ መቀነስ የሚያስችል ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በዚህም ታክሲዎች ከመደበኛ የመጫን አቅማቸው በግማሽ ቀንሰው እንዲጭኑ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን፥ 12 ሰው የመጫን አቅም ያለው ሚኒባስ ታክሲ 6 ሰው ብቻ እንዲጭኑ ተደርጓል፡፡

ሌሎች ተጨማሪ ወንበር ያላቸው እንደ ዶልፊን ታክሲዎች እንደወንበራቸው አቅም በግማሽ ቀንሰው ይጭናሉ፡፡       

የሃይገር ባስ የተሳፋሪ ቁጥር በወንበር ልኩ በግማሽ ብቻ እንዲጭኑ የተደረገ ሲሆን፥ 14 ሰው ብቻ እንዲጭኑ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ እና የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አውቶቡሶች 40 ሰው ይጭን የነበረ መደበኛ አውቶቡስ 30 ሰው ብቻ የሚጭኑ ይሆናል፡፡

ረጃጅሞቹ የተማሪ አውቶቡሶች 30 ሰው ብቻ እና አጫጭሮቹ የተማሪ አውቶቡሶች 20 ሰው ብቻ እንዲጭኑ፤ እንዲሁም ደብል ዴከር አውቶቡሶች 50 ሰው ብቻ እንዲጭን ተወስኗል፡፡ 

በመሆኑም ከነገ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቀጣይ መመሪያ እስኪሰጥ ድረስ ማንኛውም ታክሲም ሆነ ሃይገር አውቶቡስ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት በፊት እና ከምሽቱ 2:00 ሰዓት በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጥ ተደርጓል፡፡ 

በአንጻሩ የአንበሳ እና የሸገር አውቶቡሶች በተለመደው የአገልግሎት መስጫ ሰዓታቸው አገልግሎት የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡

የትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ስጦታው አካለ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት እንደተናገሩት ታክሲዎችና ሃይገር አውቶቡሶች የመጫን አቅማቸው ወደ መደበኛው እስኪመለስ ቀደም ሲል የነበረው ታሪፍ በእጥፍ አድጎ ተሳፋሪዎች እንዲከፍሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡ 

የቢሮ ሀላፊ አያይዘውም የአንበሳ እና የሸገር አውቶቡሶች ታሪፍ በነበረበት የሚቀጥል ሆኖ መንግስት በሚያደርገው ድጎማ እንዲሸፈን መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ማንኛውም በዚህ መመሪያ ከተፈቀደው ሰው በላይ ጭኖና ከተፈቀደው ሰዓት ውጭ ሲሰራ የተገኘ ታክሲም ሆነ የሃይገር አውቶቡስ ብር 5,000 (አምስት ሺህ ብር) እንደሚቀጣ አቶ ስጦታው አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የአሽከርካሪው መንጃ ፈቃድ እስከመጨረሻው እንዲታገድ በማድረግ በሌሎች የሀገሪቱ ህጎች ተጠያቂ የሚደረጉም ይሆናል ብለዋል፡፡

Leave a Reply