የትራፊክ አደጋ ቦታ ካርታ በአግባቡ መዘጋጀት የትራፊክ ግጭትን መቀነስ ያስችላል ተባለ

የትራፊክ አደጋ ቦታ ካርታ በአግባቡ መዘጋጀት የትራፊክ ግጭትን መቀነስ ያስችላል ተባለ

የትራፊክ አደጋ ቦታ ካርታ በአግባቡ መዘጋጀት የትራፊክ ግጭትን መቀነስ እንደሚያስችል ተገለጸ፡፡

የትራፊክ ግጭት መረጃ መዝጋቢ ባለሙያዎች አቅም የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተነስቷል፡፡

ብሉምበርግ ኢኒሼዬቲቭ ፎር ግሎባል ሴፍቲ የትራፊክ አደጋ ቦታ ካርታ አዘገጃጀት ዙሪያ ለአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ ኮሚሽን እና ለሁሉም ክፍለ ከተሞች የፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ግጭት መረጃ መዝጋቢ ባለሙያዎች ከመስከረም 10-11/2013 ዓ.ም ለሁለት ቀን በቨርቹዋል ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ስልጠናው ጂ አይ ኤስን በመጠቀም የትራፊክ ግጭት የሚከሰትባቸው ቦታዎችን በመለየት በሚገኘው መረጃ ተተርሶ ካርታ ለማዘጋጀት እገዛ ያደርጋል፡፡

በከተማዋ ግጭቱ የሚከሰትባቸው ቦታዎች ካርታ በሚገባ ሲዘጋጅ በሚሰበሰበው መረጃ መሰረት የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ያስችላል፡፡

ጂ አይ ኤስ የትራፊክ ግጭቱ መቼ እንደተከሰተ፣ ምን እንደሚመስል፣ አሁንና ከዚህ በፊት የተከሰቱ ግጭቶችን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ነባራዊ ሁኔታዎችን መለየት ያስችላል፡፡

በብሉምበርግ ኢኒሼዬቲቭ ፎር ግሎባል ሴፍቲ የመንገድ ደህንነት መረጃ አስተባባሪ ወ/ሮ ሜሮን ጌታቸው የትራፊክ አደጋ ቦታ ካርታ አዘገጃጀት ስልጠና በከተማዋ የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋ መረጃዎችን በአግባቡ መመዝገብ ያስችላል ብለዋል፡፡

አክለውም ግጭቱን ለመቀነስ የተደራጁ መረጃዎችን መነሻ በማድረግ በሚመለከታቸው አካላት የእርምት ማስተካከያ እንዲወስዱ እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም የትራፊክ ግጭትን ለመቀነስ የትራፊክ ግጭት መረጃ መዝጋቢ ባለሙያዎች አቅም የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ወ/ሮ ሜሮን ገልጸዋል፡፡

በመዲናችን በየዕለቱ በአማካይ ከአንድ ሰው በላይ የሞት አደጋ የሚከሰት ሲሆን፥ ከሰባት ያላነሱት ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት የደህንነት ህግ በሆኑት ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ የመቀመጫ ቀበቶ እና የግጭት መከላከያ ኮፊያ እንዲሁም ሌሎች ዋና ዋና የአደጋ መንስኤዎች ላይ እርምጃዎች በመወሰዳቸው በተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡

Leave a Reply